Exodus 33

1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አንተና ከግብፅ ያወጣኸው ሕዝብህ ይህን ስፍራ ለቅቃችሁ ‘ለዘርህ እሰጣለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ገባሁላችሁ ምድር ሂዱ። 2መልአክን በፊትህ በመላክ፣ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያዊያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ። 3ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሄድም።”

4ሕዝቡም እነዚህን አሳዛኝ ቃላት በሰሙ ጊዜ ይተክዙ ጀመር፤ ማንም ሰው አንዳች ጌጥ አላደረገም። 5እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “እስራኤላውያንን፣ ‘እናንተ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዳፍታ እንኳ ከእናንተ ጋር አብሬአችሁ ብሄድ አጠፋችሁ ነበር፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አውልቁ፤ እናንተን ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለው። 6ስለዚህ እስራኤላውያን በኮሬብ ተራራ ላይ ጌጣጌጦቻቸውን አወለቁ።

የመገናኛው ድንኳን

7ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን (ያህዌ) መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር። 8ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይጠባበቁ ነበር። 9ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር። 10ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር። 11ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር።

ሙሴና የእግዚአብሔር ክብር

12ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋር የምትልከው ማን እንደ ሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም ዐውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር። 13በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።”

14 እግዚአብሔር (ያህዌ) “ሀልዎቴ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ።

15ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋር ካልሄደ ከዚህ አትስደደን። 16አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?”

17 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው።

18ከዚያም ሙሴ “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” አለው።

19 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐውጃለሁ፤ ለምምረው ምሕረት አደርጋለሁ፤ ለምራራለትም ርኅራኄ አደርጋለሁ፤ 20ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።”

21ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤ 22ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ 23ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን መታየት የለበትም።”

Copyright information for AmhNASV